Deuteronomy 7

አሕዛብን ማስወጣት

1አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣ 2አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው
በዚህና በቍጥር 26 ላይ የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።
፤ ከእነርሱ ጋር አትዋዋል፤ አትራራላቸውም።
3ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ 4ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው። 5እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን
እዚህ ላይና በዚሁ መጽሐፍ በሌላ ስፍራ አሼራ የምትባለውን ጣዖት ምስል የሚያመለክት ነው።
ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።
6አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።

7 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቍጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር። 8ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ስለ ወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው። 9ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምላክ (ኤሎሂም) መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ (ኤሎሂም) ነው። 10ነገር ግን፣ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ይበቀላቸዋል፤ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ለመበቀል አይዘገይም። 11ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ።

12እነዚህን ሕግጋት ብታዳምጥና በጥንቃቄ ብትጠብቃቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ከአንተ ጋር የገባውን የፍቅር ኪዳኑን ይጠብቃል። 13ይወድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል። 14ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም። 15እግዚአብሔር (ያህዌ) ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብፅ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም። 16አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።

17“እነዚህ አሕዛብ ከእኛ ይልቅ ጠንካሮች ስለ ሆኑ፣ እንዴት አድርገን እናስወጣቸዋለን?” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል።

18ነገር ግን አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ላይ ያደረገውን በሚገባ አስታውስ። 19ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል። 20ይልቁንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሕይወት ተርፈው፣ ከአንተ የተደበቁት እንኳ እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ተርብ ይሰድድባቸዋል። 21በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ (ኤሎሂም) ስለሆነ አያስደንግጡህ። 22አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊቱ ቍጥር በአካባቢህ እንዳይበራከት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይፈቀድልህም፤ 23አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ግን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ትርምስ ፈጥሮባቸው በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል። 24ነገሥታታቸውን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ። እስክትደመስሳቸው ድረስ አንተን መቋቋም የሚችል አንድም ሰው የለም። 25የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ስለሆነ ያሰናክልሃል። 26አስጸያፊ ነገርን ወደ ቤትህ ወይም ወደ ራስህ አታምጣ፤ አለዚያ አንተም እንደ እርሱ ለጥፋት ትዳረጋለህ፤ ፈጽመህ ጥላው፤ ተጸየፈውም፤ ለጥፋት የተለየ ነውና።

Copyright information for AmhNASV